Saturday, May 6, 2017

ስታዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፉ ግጥም ብሎ ሞልቷል፡፡



ስታዲየሙ ከአፍ እስከ ገደፉ ግጥም ብሎ ሞልቷል፡፡ ንጋት ላይ ደምቃ የወጣችው ጸሀይ ሲያረፋፍድ ክርር ማለት ጀምራለች፡፡ ከቀኑ 4፡00 ሰዓት፡፡ ቦታው በወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ የሚገኘው የወላይታ ሶዶ ስታዲየም ነው፡፡
ስታድየሙን የሞሉ የአካባቢው ሰዎች የተሰበሰቡት ባንድ ትልቅ የጋራ ጉዳይ ነውና የጸሀይዋ መድመቅ፣ መክረርና የወበቁ ማየል ግድ አልሰጣቸውም፡፡
መሰናዶው እንዲጀመር የተቆረጠለት ሰዓት 2፡30 ቢሆንም መርሃ ግብሩ ሰዓት በመጓተቱ ምክንያት የጠቆረ ፊትና የሚነጫነጭ ስሜት አይታይም ፡፡
እስኪጀምር ማቆያ ይሆን ዘንድ ሟሟሻ ከመድረኩ አንድ ሁለት ሙዚቃዎች ለታዳሚያን ይቀርባሉ፡፡
ስታዲየሙን የሞላው ህዝብ ዘፈኑን ከስሜቱ ጋር እያዋሃደ ለመንፈሱ ፍሰሃን ይፈጥራል፡፡
ሙዚቃው ቆም ሲል ደግሞ ያለመሰልቸት የአድናቆት ድጋፋቸውን ሁለት እጃቸውን በሃይል እያላተሙ የሚገልጹት በስታዲየሙ የታደሙ ሁሉም ናቸው፡፡
መድረኩ አሁንም በባህላዊ ሙዚቃ ደምቋል፡፡ የወላይትኛ ሙዚቃ ከመሳሪያው ድምፅ ጋር ሲዋሃድ ድፍን ስታዲየሙ ተነቃነቀ፡፡
ድንቅ የባህል ኪነት፣ ዓይን ከድኖ ለመክፈት ጊዜ የማይሰጥ ጭፈራ ልዩ ድባብ ሰጥቶታል ።
ህዝቡ ባለበት በጋራ ይጨፍራል፡፡ የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችም በሙዚቃው ሃይል ተሸንፈዋል ። ተቃቅፈው ስሜታቸውን ገልጸውበታል፡፡
ከተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች የመጡ ፈረሰኞች ስታዲየሙን በግልቢያ አድምቀው የተለየ ድባብ አላበሱት፡፡
የክልሉን ማርሽ ባንድ ጨምሮ የሰራዊት ሃይሎች በዥንጉርጉር ደንብ ልብሳቸው የተለየ ውህድ ፈጥረው ለዝግጅቱ ሌላ ውበት ሰጡት፡፡
ይህንን ተከትሎ ባለፎቅ መኪና ግርማ ሞገስ ተላብሶና አሸብርቆ ወደ ስታድየሙ ሰተት እያለ ገባ፡፡
ሁሉም ቆሞ እያጨበጨና እልልታ እየሰጠ ተቀበለው ‹‹የአንድነት መቀነት›› የሆነውን የአባይን የህዳሴ ግድብ ዋንጫ ቁንጮው ላይ ያስቀመጠው ባለፎቁ መኪና በስታድየሙ ተንጎማለለ፡፡
ስታዲየሙን ድብልቅልቅ ያደረገው ድባብ እንደገና በጸጥታ ተውጦ ዋንጫው በክብር ወርዶ በወላይታ ቆነጃጅት ታጅቦ በተዘጋጀለት ቦታ ተሰየመ፡፡
የሁላችንም የመሰብሰብ ሚስጢር ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫ ህዳሴ ግድብ መሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ ዓመት በዓል፡፡
በዓሉ የተከበረው ‹‹የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የአገራችን ህብር ዜማ የህዳሴያችን ማማ ›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡
በዓሉ የተከበረበት የወላይታ ዞን በክልሉ የሚገኘውን የህዳሴ ዋንጫ የተረከበበት ሳምንት በመሆኑ ለበዓሉ የተለየ ድምቀት ፈጥሯል፡፡
የህዳሴ ዋንጫ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ሲዘዋወር ዛሬም ድረስ ያልቀዘቀዘውን ግለት የተመለከተ ሰው እውነትም ግድቡ የህብር ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ ነው›› ይላል፡፡ ሁሉም በተመስጦ ያዜምለታልና፡፡
ህዝቡ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ልዕልና እና ቸ ገናና ስልጣኔ ወደ አሳፋሪ ተመጽዋችነት የወረደችበትን የታሪክ ገጽታ በመፋቅ አዲስ አቅጣጫ፣ አዲስ ራዕይና አዲስ አስተሳሰብ ለመያዝ ለአንድ አላማ አብሯል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ልጆች ለጋራ ጉዳያቸው በጋራ መቆም እንደሚችሉ ያሳየ ተምሳሌት ነው፡፡ የ‹‹አይቻልም›› አስተሳሰብንም በ‹‹ይቻላል›› የተካ የህዳሴ መሰረት፡፡
የአክሱምን ስልጣኔ የነላሊበላን ጥበብ፣ የአድዋን ጀግንነት ድህነትን ድል በመንሳት ታሪክ ለመድገም ቆርጠዋልና አባይና አባይን በሚመለከቱ ጉዳዮች በጋራ አንድ ዓይነት ድምጽ ያሰማሉ፡፡
ዋንጫው በሚዘዋወርባቸው አካባቢዎች የተፈጠረው ስሜት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ያጠናከረና የባህል አምባ በሆነው ደቡብ ህብረብሄራዊነታቸው የሚገለጽበትና የአንድነታቸው ማጠናከሪያ መሆኑን ያሳየ ነው፡፡
በእለቱ ዋንጫውን የተረካከቡ የወላይታና የሀድያ የአገር ሽማግሌዎች በተለዋወጧቸው ስጦታዎች አማካይነት ፍቅራቸውን ፣ መተሳሰባቸውንና አንድነታቸውን ገልጸውበታል፡፡
የሃገር ሽማግሌዎቹ የህዳሴው ግድብ የመተሳሰባችንና የመደጋገፋችን የአንድነታችንም ፍኖት ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት የደቡብ ብሄር ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬ “ታላቁ የህዳሴ ግድብ የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣና አንድነት እያጠናከረ የሚገኝ የአዲስቷ ኢትዮጵያ የጋራ ምልክት ነው" ብለዋል፡፡
የክልሉ ህዝብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገው ድጋፍና ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው ለጋራ ተጠቃሚነት ሲባል መስዋዕትነት የሚከፍልና ታሪክ የሚሠራ ትውልድ እየተፈጠረ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በሃገሪቱ የተፈጠረው ስርዓት ህብረ ብሄራዊነትንና ብዙሃነትን ማሰተናገዱ መላው የክልሉና የኢትዮጵያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች በጋራ የሚረባረቡበትን እድል በመፍጠሩ በራስ አቅም ትልልቅ ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
ዋንጫው በክልሉ ከገባበት ቀን ጀምሮ ህዝቡ እያደረገ ያለው ከፍተኛ ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ ደሴ ህዝቡ ለግድቡ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
በዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ዋንጫውን የተረከበው የደቡብ ክልል ዋንጫው በክልሉ በሚያደረገው የአንድ አመት ቆይታ 500 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ቢንቀሳቀስም ገና በአራት ወር ቆያታው ብቻ 522 ሚሊየን ብር ተሰብስቧል ።
የደቡብ ህዝቦች ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ጌታቸው እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በክልሉ ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ነው የገለፁት፡፡
ዋንጫው ወደ ክልል ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ መነቃቃት በመፈጠሩ የህብረተሰቡ የገቢ ማሰባሰሰብ ተሳትፎ እያደገ መጥቷል፡፡
እንደ አቶ ፋሲካ ገለጻ ሁሉንም ህብረተሰብ በየደረጃው ለማሳተፍ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያመጣ በመሆኑ ዋንጫው ለአንድ ዓመት በክልሉ በሚኖረው ቆይታ የተሻለ ገቢ ይሰበሰባል፡፡
አሁን ዋንጫው በሚገኝበት በወላይታ ዞን በ10 ቀናት የዋንጫው ቆይታ ብቻ 202 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን የተናገሩት የወላይታ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አስራት ጤራ ከገንዘቡ በተጨማሪ በስጦታ የተበረከቱ ሰንጋ በሬዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በቀሪ ቀናትም ተጨማሪ ገቢ ይሰበሳበል ያሉት አስተዳዳሪው በግድቡ ግንባታ በየደረጃው ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ የንቅናቄ መድረክ ይፈጠራል ብለዋል፡፡
በንግድ ስራ የተሰማሩት የሶዶ ከተማ ነዋሪው አቶ ያዕቆብ አልታዬ " በራሳችን አቅም የምንሰራው የግድቡ ግንባታ ከግማሽ በላይ ተጠናቆ ስድስተኛ ዓመቱን ስናከብር ታላቅ ደስታ ይሰማኛል" ብለዋል፡፡
ግንባታው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ከሶስት ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ያዕቆብ ዋንጫው ዞኑ በገባበት ወቅትም በተጨማሪ ከአንድ ሚሊየን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ያዕቆብ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
ሌላኛው ወጣት ተሾመ ተክሌ በተለያዩ ጊዜያት እስከ 90 ሺህ ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፉን ያበረከተ ሲሆን በአባይ ዙሪያ የንቅናቄ መድረኮች ሲፈጠሩ በማስተባበር ይታወቃል፡፡
ግድቡ ለዚህ ትውልድ የተፈጠረ አዲስ እድል በመሆኑ ሃይል ማመንጨት እስኪጀምር በጉልበት፣በገንዘብና በእውቀት የበኩሉን እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡

ምንጭ (ኢዜአ) 

No comments:

Post a Comment